የኮረና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋትን ተከትሎ መንግስት ያስቀመጠውን የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ፍቃደኛ ያልሆኑ አራት ትምህርት ቤቶች ለአንድ አመት የእውቅና ፍቃዳቸው መታገዱን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ ጉዳዩን አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ አለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነው የኮረና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋትን ተከትሎ የኢ.ፌ.ድ.ሪ. ትምህርት ሚኒስተር ከመጋቢት 7/2012 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ በወሰነው መሰረት በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች የትምህርት አገልግሎታቸውን በተለያዩ መንገዶች እንዲሰጡና የሚያስከፍሉት የአገልግሎት ክፍያም ከ50 እስከ 75 ፐርሰንት እንዲሆን መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
ወይዘሮ ሸዊት አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መመሪያው ተግባራዊ መሆኑን በትምህርት ቤቶቹ ክትትል ማድረጉንና አብዛኞቹ በወረደው መመሪያ መሰረት ተገቢውን ክፍያ በማስከፈል ላይ መሆናቸውን በመግለጽ 21 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ከመመሪያው ውጪ ተገቢ ያልሆነ ክፍያ በመጠየቃቸው በአንድ ሳምንት ውስጥ ማስተካከያ እንዲያደርጉ በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ መሰረት 17 የሚሆኑት ማስተካከላቸውን ጠቁመው ቀሪዎቹ 4 ትምህርት ቤቶች ግን የክፍያ መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ፍቃደኛ ስላልሆኑ በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አገልግሎት እንዳይሰጡ ለአንድ አመት እውቅና ፍቃዳቸው መታገዱን አስታውቀዋል፡፡
ፍቃዳቸው የታገደባቸው ትምህርት ቤቶች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኙት ለምለም እና ሮማን ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የካ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ስሪ ኤም አካዳሚ ና አራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ገነት መሰረተ ክርስቶስ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን በመግለጫው ጠቅሰዋል፡፡
መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የዩቲዩብ ፣ የቴሌግራም ፣ የፊስቡክ እና የትዊተር ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
You Tube: https://www.youtube.com/watch?v=TWkBGoeYCNQ
Telegram ፡ https://t.me/wwwAddisAbabaeducationbureau
Twitter ፡ https://twitter.com/aacaebc
Facebook : https://www.facebook.com/aacityeducationcommunication
እንራራቅ፣ እንታጠብ እንዲሁም አንጨባበጥ፡፡