የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አዲሱን ስርዓተ ትምህርት መሰረት አድርጎ ተዘጋጅቶ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለዉን የተማሪዎች የመማሪያ መጽሀፍና የመምህር መምሪያን ለሚገመግሙ መምህራን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ ፡፡
የመጽሀፍ ግምገማው ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች በውጤታቸውና ስነ-ምግባራቸው በተመረጡ መምህራንና በቢሮው ስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ባለሙያዎች በአማርኛ እና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች በየትምህር አይነቱ በእቴጌ መነን አዳሪ ትምህርት ቤት እስከ ምሽቱ 4 ሰሃት ድረስ እንደሚካሄድ ከወጣው መርሀ- ግብር ለማወቅ ተችሉዋል ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በመርሀ-ግብሩ ተገኝተው በመጽሀፍ ግምገማው ለሚሳተፉ መምህራን ባስተላለፉት መልዕክት መምህራኖች በዚህ ታሪካዊ በሆነው የትውልድ ግንባታ ሂደት የበኩላቸውን አሻራ ማሳረፍ በመቻላቻው ከፍተኛ ኩራት ሊሰማቸው እንደሚገባ ገልጸው በመጽሀፍ ዝግጅቱ ከመተርጎም ጀምሮ ለሙከራ ትግበራ እስኪደርስ ኃላፊነታቸውን ለተወጡ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም የግምገማው ተሳታፊዎች መጽሀፍቱ በሙከራ ደረጃ ሲተገበሩ የነበሩ ጠንካራና መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች በአግባቡ በመለየት እንዲሁም በሁለተኛ መንፈቅ አመት በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ የሚደረጉትን ይዘቶች በዝርዝር በማየት ወደ ሙሉ ትግበራ ለመግባት በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ደቻሳ በበኩላቸው አዲሱን ስርዓተ ትምህርት መሰረት አድርጎ የተዘጋጀው የተማሪዎች የመማሪያ መጽሀፍም ሆነ የመምህር መምሪያ ወደ አማርኛ እና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች ከመተርጎም ጀምሮ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት በማስገምገም በ44 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸው በአዲስ አበባ ደረጃ ከዚህ ተግባር ጋር በተገናኘ የተከናወኑ ተግባራት ለተለያዩ ክልሎች ጭምር እንደተሞክሮ እየተወሰዱ እንደሚገኝ በመግለጽ በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በአዲስ አበባ ደረጃ መጽሀፍቱ ታትመው ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲገቡ ለማስቻል የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
የቢሮው የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ጌታቸው ታለማ እና የአፋን ኦሮሞ ስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ትግበራና አጠቃላይ ሱፐርቪዝን ዳይሬክቶሬት ባለሙያው አቶ ገመቺስ ፍቃዱ ገምጋሚዎቹ መጽሀፍቱን ይዘት በሚገመግሙበት ወቅት ሊከተሉዋቸው በሚገቡ አሰራሮች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡
መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት ማሰፈንጠሪያዎቹን ይጫኑ!
You Tube: https://www.youtube.com/watch?v=TWkBGoeYCNQ…
Telegram ፡ https://t.me/wwwAddisAbabaeducationbureau
Twitter ፡ https://twitter.com/aacaebc
Face book: https://www.facebook.com/aacityeducationcommunication
Blog: – http://www.aacaebc.wordpress.com/
Website: – aaceb.gov.et
Email;- aacaebc@gmail.com
Instagram: – https://www.instagram.com/aacaeb/
ባልታጠበ እጅ አይንዎን አፍዎን እና አፍንጫዎን ባለመንካት በዙሪያዎ ላሉ ሰዎች አርአያ ይሁኑ!


