የአማርኛ የሬዲዮ ትምህርት ጽሑፍ (ስክሪፕት) ግምገማ ተካሄደ

DSC_7454

 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የሬዲዮና ትምህርት አጠቃላይ አድማጮች ፕሮግራም ዝግጅት ንዑስ የስራ ሂደት ወደ 150 የሚጠጉ ከተመረጡ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ መምህራንን፣ የክላስተር ሱፐርቫይዘሮችን እና የቢሮ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ከፍል የአማርኛ የሬዲዮ ትምህርት ስክሪፕት(ፅሑፍ) ግምገማ አካሄደ፡፡

የሬዲዮ ትምህርት አጠቃላይ አድማጮች ፕሮግራም ዝግጅት ንዑስ የስራ ሂደት መሪ አቶ አብይ ተፈራ  በዝግጅቱ ወቅት እንደገለፁት ስክሪፕቶቹን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሲገመገሙ ፅሑፎቹ ያለባቸውን ጉድለት  እና ጠንካራ ጎን በመለየት ግብዓት ለማግኘት ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀው ስክሪፕቱ መገምገሙ የተሟላና ተማሪዎችን የሚመጥን እንዲሆን ይረዳል ብለዋል፡፡

የሬዲዮ ትምህርት ስክሪፕት (ፅሑፉ) በቡድን በመሆን  ከመገምገሙ በፊት  የሬዲዮ ትምህርት ፅሑፍ  ምን ማለት እንደሆነ ፣ እንዴት እንደሚፃፍ በአዘጋጆቹ ተብራርቷል፡፡ ከግምገማው በኋላም በቡድን በመሆን የተገመገሙት የሬዲዮ ፅሑፎቹ በተወካዮች የቀረበ ሲሆን ስክሮፕቶቹ የመማሪያ መፅሐፍቱን መሰረት አድረገው መዘጋጀታቸው ፣የቃላት አጠቃቀማቸው መደበኛ መሆኑ ፣ተማሪዎችን አሳታፊ መሆናቸው እና እንደተጨማሪ የማስተማሪ ዘዴ ተማሪዎች ትምህርቱን በተሻለ መንገድ እንዲረዱት  ማድረግ መቻሉ በጠንካራ ጎኑ የቀረቡ ሲሆኑ  የስክሪፕቶቹ ይዘት ተመሳሳይ መሆኑ፣ ብዙ ሀሳቦች በአንድ ስክሪፕት ላይ መታጨቃቸው፣ አብዛኛዎቹ ስክሪፕቶች  ከመመሪያ መፅሐፍቱ በቀጥታ የተወሰዱ  መሆናቸው በግምገማው ከታዮ ደካማ ጎኖች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በስክሪፕት ግምገማው  በጽሑፍ ላይ ሊስተካከሉ የሚገቡ ጉዳዮች እንዲስተካከሉና ድጋሚ መታየት ያለባቸው በድጋሚ ታይቶ ለህፃናቱ በሚመች ሁኔታ ሊቀርብ እንደሚገባ ተሳታፊዎች  አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የተዘጋጀው የአማርኛ ትምህርት የሬዲዮ ስክሪፕት በቢሮው ሬዲዮና ትምህርት አጠቃላይ አድማጮች ፕሮግራም ዝግጅት ንዑስ የስራ ሂደትና በስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዋና የሥራ ሂደት ባለሙያዎች የተዘጋጀ መሆኑን አቶ አብይ ተፈራ ለኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የስራ ሂደት ገልፀዋል፡፡