የርዕሳነ መምህራንና የትምህርት ሱፐርቫዘሮች ውይይት ተካሄደ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበላይ አመራሮች በተገኙበት ርዕሳነ መምህራንና የትምህርት ሱፐርቫይዘሮች በወቅታዊው የትምህርት ቤቶች ጉዳይ ዙሪያ ውይይት አካሄዱ፡፡
በዚህ ውይይት ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት ብዝሀ ቋንቋ ሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ በመሆኑ ሕዝቡና ባለደርሻ አካላት ተወያይተውበት ዳብሮ ከጸደቀ በኋላ ተግባራዊ ይደረጋል ያሉት ክብርት ከንቲባ በተማሪዎች መካከል አለመተማመንና መከፋፈልንና መገፋፋትን የሚሰብኩ ሰዎች ከዚህ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በአዲስአበባ 557 ከመንግስት ትምህርት ቤቶች በ18ቱ ትምህርት ቤቶች የፈጠረው ሁከት የሰው ህይወት ሳይጠፋና ብዙ ጉዳት ሳይደርስ መቆጣጠር መቻሉንና በቀጣይ የመማር ማስተማሩ ሂደት ፍፁም ሰላማዊና የተረጋጋ እንዲሆን በትጋት እየሰሩ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡
ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ተማሪዎችን በብሔር የመክፋፈል ዝንባሌ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚጎዳ በመሆኑ ሊታረም ይገባዋል ብለዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ብሔርንና ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ ተማሪዎችንና ወላጆችን ተሳታፊ በማድርግ አዲስ አበባ ከተማን የብጥብጥና የትርምስ ማዕከል ለማድረግ ጽንፈኛ ኃሎች ያሴሩት ሴራ በትምህርት አመራሩ ፣በመምህራንና በተማሪዎች፣ በወላጆችና በአመራሩ የተቀናጀ ስራ መከሸፉን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ስራ የላቀ ትኩረት በመስጠት ከፍተኛ በጀት መድቦ ተማሪዎች በዕውቀትና በስነ-ምግባር ታንጸው ብቁ ዜጋ መሆን እንዲችሉ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው በገለጻቸው ብዝሀ ማንነትን የምታስተናግደው አዲስ አበባ ከተማ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማሯ ዓለም አቀፋዊ፣ ሕገ መንገስታዊና ሰብዓዊ መብት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሰሞኑን በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የታየው ድርጊት ይህን መብት የሚጋፋ በመሆኑ መታረም ያለበት መሆኑን ገልጸው መንግስት ትምህርት ቤቶች ከማናቸውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ነጻ ሆነው የመማር ማስተማር ስራቸውን እንዲያከናውኑ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባሎቻቸውን በማሰማራት ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ መቀስቀሳቸው በማስረጃ መረጋገጡን አብራርተው ሕጋዊ ተጠያቂነት ለማስፍን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የስብሰባው ተሳተፊ ርዕሰ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮችና በበኩላቸው ዜጎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር መብታቸው መከበሩ ሕገ መንግስታዊና ሰብዓዊ መብት መሆኑና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአምስት አመታት በፊት ትምህርት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
በትምህርት ቤቶች እያጋጠመ ያለው ችግር ለዘመናት የቆዩ የጥላቻ ትርክት ውጤት መሆኑን ተወያዮቹ ያነሱ ሲሆን ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
እንደ ትምህርት ባለሙያዎቹ ገለፃ ገዥው ፓርቲ ከትምህርት ቤቶች ትምህርት ነፃ መሆን አለበት ብሎ ሲወጣ በተቃራኒው ሌሎች ገብተዋልና ይሄንን አጥርቶ መንግስት እንዲያጠራ አሳስበዋል፡፡
የተለያዩ ጥያቄዎች ቢኖሩም በፍፁም ይህ ጉዳይ ሊያጋጭና ወደ ብጥብጥ ሊያመራ የማይችል መሆኑን አንስተዋል፡፡
በትምህርት ቤት ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ ተልዕኮ የተሰጣቸው ተማሪዎች መኖራቸውንና ከውጪ ድንጋይ በመወርወርና በር ገንጥለው በመግባት ተቀናጀተው የሰሩት ስራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በተማሪዎች መካከል መጠራጠርና አለመግባባት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ሐሰተኛ መረጃዎችንና ቅስቀሳዎችን የሚያሰራጩ ግለሰቦችንና ተቋማትን መንግስት ተጠያቂ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
በተጨማሪም አንዳንድ የምክር ቤት አባላት በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን የተሳሳተ መረጃ እየሰጡ ወላጆች መንግስትን እንዲጠራጠር እየሰሩ በመሆኑ በህግ ተጠያቂ ይደረጉ ብለዋል ፡፡
መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት ማሰፈንጠሪያዎቹን ይጫኑ!
TikTok፡- tiktok.com/@aaeducationbureau
You Tube: https://www.youtube.com/watch?v=TWkBGoeYCNQ…
Telegram ፡ https://t.me/wwwAddisAbabaeducationbureau
Twitter ፡ https://twitter.com/aacaebc
Face book: https://www.facebook.com/aacityeducationcommunication
Blog: – http://www.aacaebc.wordpress.com/
Website: – aaceb.gov.et
Email;- aacaebc@gmail.com
Instagram: – https://www.instagram.com/aacaeb/