በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አዲሱን ስርዓተ ትምህርት መሰረት አድርጎ ተዘጋጅቶ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገው የተማሪዎች የመማሪያ መጽሀፍና የመምህር መምሪያ ግምገማ በጥሩ ሁኔታ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
የመጽሀፍ ግምገማው ከ17/06/2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሙከራ ትግበራው ከሚካሄድባቸው ትምህርት ቤቶች በተመረጡ መምህራንና በመጽሀፍ ዝግጅቱ ተሳታፊ በነበሩ መምህራን እንዲሁም በቢሮው የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ባለሙያዎች በየትምህርት አይነቱ በአማርኛ እና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች በእቴጌ መነን የሴት ተማሪዎች አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ጌታቸው ታለማ የመጽሀፍ ግምገማ ሂደቱን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት አዲሱን ስርዓተ ትምህርት መሰረት አድርጎ ተዘጋጅቶ በአዲስ አበባ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘውን የተማሪዎች የመማሪያ መጽሀፍም ሆነ የመምህር መምሪያ አተገባበርን በተመለከተ በየትምህርት ቤቱ የተካሄደ ምልከታን መሰረት በማድረግ ግምገማው በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው እስካሁን ባለው ሂደትም ገምጋሚ መምህራኑ በተዘጋጀላቸው የመገምገሚያ መስፈርት መሰረት መጽሀፍቱን በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በአግባቡ እየገመገሙ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የአፋን ኦሮሞ ስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ትግበራና አጠቃላይ ሱፐርቪዝን ዳይሬክቶሬት ባለሙያው አቶ ተሾመ ደገፋ በበኩላቸው አዲሱን ስርዓተ ትምህርት መሰረት አድርጎ የተዘጋጀው የተማሪዎች የመማሪያ መጽሀፍም ሆነ የመምህር መምሪያ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ በተደረገባቸው ትምህርት ቤቶች በቢሮው ባለሙያዎች አስፈላጊው የድጋፍና ክትትል ስራ ተሰርቶ ወደ ግምገማው መገባቱን ገልጸው የግምምገማው ሂደትም ከጥዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የመጽሀፍ ግምገማው በአማርኛው ስርዓተ ትምህርት በ7 የትምህርት አይነቶች እንዲሁም በአፋን ኦሮሞ ስርዓተ ትምህርት በ8 የትምህርት አይነቶች በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን በግምገማ ሂደቱ የሚገኙ የማስተካከያ ሀሳቦችን በማካተት መጽሀፍቱ ታትመው በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ወደ ሙሉ ትግበራ ለመግባት እየተሰራ እንደሚገኝ ቀደም ተብሎ መገለጹ ይታወቃል፡፡
መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት ማሰፈንጠሪያዎቹን ይጫኑ!
You Tube: https://www.youtube.com/watch?v=TWkBGoeYCNQ…
Telegram ፡ https://t.me/wwwAddisAbabaeducationbureau
Twitter ፡ https://twitter.com/aacaebc
Face book: https://www.facebook.com/aacityeducationcommunication
Blog: – http://www.aacaebc.wordpress.com/
Website: – aaceb.gov.et
Email;- aacaebc@gmail.com
Instagram: – https://www.instagram.com/aacaeb/
ባልታጠበ እጅ አይንዎን አፍዎን እና አፍንጫዎን ባለመንካት በዙሪያዎ ላሉ ሰዎች አርአያ ይሁኑ!
